የአቶ ታኬት አስፋው የቀብር ስነስርአት ተፈጸመ

 (GCDC) - ነሐሴ 28/2009 /ኢዜአ/ነሐሴ 28/2009 /ኢዜአ/የጋምቤላ ሕዝቦች ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ምክር ቤት ዋና አፈ- ጉባኤ የነበሩት የአቶ ታኬት አስፋው የቀብር ስነስርአት ተፈጸመ።

የአቶ ታኬት አስፈው ስርዓተ ቀብር ትናንት የተፈጸመው ቤተሰብ፣ ወዳጅ ዘመድና የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት በትውልድ ስፍራቸው መንጌሽ ወረዳ አስኔ ቀበሌ ነው።... በስርዓተ ቀብራቸው ላይ የተነበበው የሕይወት ታሪካቸው እንደሚያስረዳው አቶ ታኬት አስፋው ከአባታቸው ከአቶ አስፋው አምበሉና ከእናታቸው ከወይዘሮ ሜላንኮይ ጎጃን 1968 . በሲሪ ማጃንግ ቀበሌ ነው የተወለዱት። ዕድሚያቸው ለትምህርት ሲደርስ በሲሪ ማጃንግ፣ በአበሪ ሜጢ፣ በአሽኔና በኩሜ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን ተከታትለዋል። አቶ ታኬት አስፋው የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን አዲስ አበባ በሚገኘው አዳሪ ትምህርት ቤት ተከታትለዋል። በዚህም ለከፍተኛ ትምህርት መግቢያ ውጤት አምጥተው 1998 . ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በመግባት በቢዝነስ ትምህርት የመጀመሪያ ድግሪያቸውን አግኝተዋል።

እንዲሁም በነበራቸው ከፍተኛ የትምህርት ፍላጎት በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ በህዝብ ፋይናንስ አስተዳደር ሁለተኛ ድግሪያቸውን ተቀብለው ነበር። አቶ ታኬት አስፋው በስራ ዘመናቸውም በኦፔኖ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ በምምህርነት፣ በክልሉ ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ደግሞ በቢሮ ኃላፊነት አገልግለዋል። በአራተኛው ዙር ሀገር አቀፍ ምርጫም የክልሉን ህዝብ በመወካል ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተወዳድረው በማሸነፍ ለአምስት ዓመት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል በመሆን ሰርተዋል። እንዲሁም በአምስተኛው ዙር ሀገር አቀፍ ምርጫ ለክልል ምክር ቤት አባልነት ተወዳድረው በማሸነፍ ከሐምሌ 2007 ጀምሮ እስከ እልፈተ ህይወታቸው ድረስ የክልሉ ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ሆነው አገልግለዋል። አቶ ታኬት አስፋው ባደረባቸው ሕመም በሕክምና ሲረዱ ከቆዩ በኋላ ነሐሴ 26 ቀን 2009 ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩ ሲሆን ባለትዳርና የሦስት ሴት ልጆች አባት ነበሩ። በስርዓተ ቀብራቸው ላይ የተገኙት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጋትሉዋክ ቱት እንዳሉት አቶ ታኬት አስፋው ክልሉ ካፈራቸው ታላላቅ የሕዝብ ልጆች አንዱ ናቸው። ህገ- መንግስቱ ያረጋገጠው የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች መብት እንዲከበር ኃላፊነታቸውን የተወጡ አመራር እንደነበሩም ተናግረዋል።

"የተከበሩ አቶ ታኬት አስፋው በሥነ -ምግባራቸው ምስጉንና የተሰጣቸውን ኃላፊነት ከስራ ባልደረቦቻቸው ጋር ተግባብተው የሚወጡ ሲሆን በትምህርት ያካበቱትን ዕውቀትና ልምድ ለሕዝብ ጥቅም ብቻ ለማዋል ሲሰሩ የነበሩ አመራር ነበሩ" ብለዋል። በሰሩባቸው መስሪያቤቶች ውስጥ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች መንግስት ባስቀመጣቸው አቅጣጫ ብቻ እንዲፈጸሙና የህዝብ ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ በሙሉ አቅማቸው ያገለገሉ ታታሪ አመራር እንደንነበሩም ተናግረዋል። አሁን ካገለገሉት ሕዝብና የትግል አጋሮቻቸው በሕይወት ቢለዩም የነበራቸው ራዕይ መቼም ጊዜ የማይረሳና በተተኪ አመራሮች የሚፈጸም መሆኑን አቶ ጋትሉዋክ ተናግረዋል። በመጨረሻም ለተከበሩ አቶ ታኬት አስፋው ቤተሰቦች፣ ወዳጆችና የትግል አጋሮች በክልሉ መንግስት ስም መጽናናትን ተመኝተዋል።