አዲስ አበባ ,መስከረም 7/2010 (GCDC) - በጋምቤላ ክልል ቤተሰቦቻቸው ከደቡብ ሱዳን በመጡ የሙርሌ ታጣቂዎች የተገደሉባቸው ህፃናትን በዘላቂነት ለማቋቋም ሁሉም የአጋርነት ሚናውን እንዲወጣ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ ጠየቁ።

ህፃናቱን ለማቋቋም በብሔራዊ ቤተ መንግስት በተደረገው የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር 75 ሚሊዮን ብር በላይ በገንዘብና በአይነት ድጋፍ ለማድረግ ቃል ተገብቷል።

ከደቡብ ሱዳን የመጡት እነዚህ ታጣቂዎች ሚያዚያ 2008 . በጋምቤላ ክልል በአኙዋክና በኑዌር ብሄረሰብ  ላይ በሰው ህይወትና በንብረት ላይ ጉዳት ማድረሳቸው ይታወሳል።

ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ በዚህ ወቅት እንደተናገሩት እነዚህ ወላጆቻቸውን በጥቃቱ ያጡ ህፃናት ከደረሰባቸው የሥነ ልቦናና ማህበራዊ ቀውስ በማውጣት ወደ ቀድሞ ሰላማዊ ኑሯቸው ለመመለስ የህዝብና የመንግስት ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል።

ተጎጅዎችን ከማገዝና ከመደገፍ በላይ የህሊና እርካታ የሚያስገኝ ነገር ባለመኖሩ የጋምቤላ ወገኖቻችን ላቀረቡልን ጥሪ አፋጣኝ ምላሽ በመስጠት አለኝታችንን ማረጋገጥ አለብን ብለዋል ፕሬዚዳንቱ።

የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጋትሉዋክ ቱት ኮት በበኩላቸው ክልሉ ተጎጂዎችን ለመደገፍ ያላሰለሰ ጥረት ሲያደርግ ቢቆይም በዘላቂነት ለማቋቋም የሌሎች አካላትን ድጋፍ እንደሚያስፈልግ ነው የተናገሩት።

ርዕሰ መስተዳድሩ ህፃናቱ ብሩህ ተስፋ ይዘው አድገውና ተምረው ለአገራቸውና ለህዝባቸው የሚጠቅሙ ዜጎች እንዲሆኑ ለማድረግ የተጀመረው ድጋፍ እንዲቀጥል ጥሪ አስተላልፈዋል። (ኢዜአ)

Connect with us