አዲስ አበባ መስከረም 12/2010 (GCDC) - በጋምቤላ አውሮፕላን ማረፊያ ላይ ሲገነባ የነበረው ባለ ሰባት ፎቅ የአየር ትራፊክ መቆጣጠሪያ ማማ ግንባታ መጠናቀቁን የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን ገለጸ፡፡

ለግንባታው 32 ሚሊየን ብር ወጪ የተደረገበት የአየር ትራፊክ መቆጣጠሪያ ግንባታ ተጠናቆ መስከረም 10 ቀን 2017 . ለአየር ማረፊያው መተላለፉን ባለስልጣኑ ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታውቋል፡፡

የመቆጣጠሪያ  ማማው የሲቪል ስራ፣ የኤሌክትሪክ እና የመፀዳጃ መስመሮች ዝርጋታ እና ሌሎች የሜካኒካል ስራዎች ግንባታ ሙሉ ለሙሉ የተጠናቀቀ ሲሆን የመገናኛና የቅኝት መሳሪያዎች  እንደተገጠሙለት ስራ ይጀምራል ተብሏል ፡፡ ቀደም ሲል የነበረው ማማ ደረጃው እጅግ ዝቅ ያለና ለአሰራር ምቹ ያልነበረ ሲሆን አዲሱ ማማ  ለአስራሮች ምቹ ሁኔታን ከመፍጠር አኳያ የሚኖረው ፋይዳ የጎላ መሆኑም ተጠቅሷል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከዚህ በፊት በሳምንት ሁለትና ሶስት ጊዜ ወደ ጋምቤላ ሲያደርግ የነበረው የበረራ  ብዛት አሁን በቀን ሁለት ጊዜ ከፍ ማድረጉን በማስታወስ  አዲሱ ማማ የትራፊክ ፍሰቱን ከማቀላጠፍ ባለፈ ለሰራተኞቹ አመቺ የስራ አካባቢን ይፈጥራል፡፡

ባለስልጣኑ በቀጣይ በጎዴ፣ ባሌ ሮቤ፣ አሶሳ፣ ኮምቦልቻ፣ ሰመራ፣ ሽሬ እንደስላሴ፣ ጂንካና ሀዋሳ ኤርፖርት የሚገኙትን ጅምር የአየር ትራፊክ መቆጣጠሪያ ማማዎችን መጨረስና አዳዲስ ግንባታዎችን እንደሚጀምር አስታውቋል፡፡ (ኢዜአ)

Connect with us