ጋምቤላ, መስከረም 21,2010 (GCDC) - የጋምቤላ ህዝብ አንድነት ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ጋህአዴን ) የተጀመሩ የልማት ስራዎችን አጠናክሮ በማስቀጠል የህዝቡን ተጠቃሚነት የበለጠ ለማረጋገጥ እንደሚሰራ አስታወቀ።

ንቅናቄው ያካሄደውን ሰባተኛ ድርጅታዊ ጉባኤ የተለያዩ ውሳኔዎችን በማሳለፍና ባለ 12 ነጥብ የአቋም መግለጫ በማውጣት አጠናቋል።

ንቅናቄው ጉባኤውን ያጠናቀቀው በቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት ድርጅቱን የሚመሩ ዋናና ምክትል ሊቀመንበሮችን ጨምሮ 35 ማዕካላዊ ኮሚቴ፣ ዘጠኝ ስራ አስፈፃሚዎችና አምስት የኦዲትና የቁጥጥር ኮሚሽነሮችን በመምረጥ ነው።

እንዲሁም ድርጅቱ ባለፉት ዓመታት በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፓለቲካዊ መስኮች በተከናወኑ እቅድ አፈፃፀምና የኦዲት ሪፖርት ላይ ተወያይቶ አፅድቋል።

ጉባኤው በተጨማሪ የድርጅቱ መተዳደሪያ ደንብ ማሻሻያና የቀጣይ የልማት ትኩረት አቅጣጫዎች ዙሪያ ተወያይቶ በማጽደቅ ተጠናቋል ።

የድርጅቱ ሊቀ መንበር አቶ ጋትሉዋክ ቱት ጉባኤው ማጠናቀቂያ ላይ እንደገለጹት በቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት የህዝብ ንቅናቄ በመፍጠር የተጀመሩ የልማትና የጸረ ድህነት ትግል በማፋጠን የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በትኩረት ይሰራል።

"በክልሉ በተለይም በመንደር ማዕከላት በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች የተጀመሩ የልማት ስራዎችን አጠናክሮ በማስቀጠል ህዝቡን ተጠቃሚ የማድረጉ ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላሉ" ብለዋል ።

ሰፊ የስራ እድል በመፍጠር ወጣቶችና ሴቶችን ተጠቃሚ ለማድረግ ድርጅቱ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ በትኩረት እንደሚሰራም ሊቀ መንበሩ አስታውቀዋል።

"ባለፈው ዓመት በጥልቅ ታሀድሶ በህዝቡ ሲነሱ የነበሩ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ደረጃ በደረጃ ለመፍታት ድርጀቱ በትኩረት ይሰራል" ብለዋል አቶ ጋትሉዋክ።

የድርጅቱ አመራሮችና አባላት ወደ ህብረተሰቡ በመግባት ቀደም ሲል የተጀመሩ የልማት ስራዎች በህዝብ ተሳትፎ ውጤታማ ለማድረግ  የተጣለባቸውን ኃላፊነት በብቃት እንዲወጡ ጠይቀዋል።

የጉባኤው አባላት ባወጡት ባለ12 ነጥብ የአቋም መግለጫ በድርጅቱ ከተሃድሶ በፊት የነበሩ የጠባብነትና ብልሹ አሰራሮች ዳግም እንዳይከሰቱ በመታገል የክልሉን ልማት ለማፋጠን እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።

እንዲሁም የክልሉን የግንባታ ፕሮጀክቶች አፈጻጸምና ጥራት በማስጠበቅ፣ ወጣቱን ተጠቃሚ በማድረግ ፣ የገቢ አቅም በማሳደግና በሌሎችም የልማት ዘርፎች በትኩረት እንደሚሰሩ አመላክተዋል ።

በክልሉ ካለፈው ጥልቅ ተሃድሶ ግምገማ ወዲህ ቀደም ሲል የነበረው ጠባብ አመለካከትና ቡድኝተኝነት ተወግደው ሁሉም አመራር ወደ ስራ በመግባት የተሻለ ልማት መመዝገቡን የገለጹት ደግሞ አቶ ኡሞድ ኡጁሉ ናቸው። (ኢዜአ)

Connect with us