የጋምቤላ ክልል ምክር ቤት አስቸኳይ ጉባኤ በማካሄድ ላይ ነው

ታህሳስ 07፣2009 (GCDC) - በጋምቤላ ክልል በሕዝብ ለሚነሱ የመልካም አስተዳደርና የልማት ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት በየደረጃው የተጀመሩት ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የክልሉ ምክር ቤት አስታወቀ።

የክልሉ ምክር ቤት አምስተኛ ምርጫ ሁለተኛ የሥራ ዘመን ሁለተኛ አስቸኳይ ጉባኤ ዛሬ በጋምቤላ ከተማ ተጀምሯል።

የምክር ቤቱ ምክትል አፈ-ጉባኤ አቶ ኳንግ አኳይ ጉባኤውን ሲከፍቱ እንደገለጹት በህዝቡ የሚነሱ የመልካም አስተዳደርና የልማት ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት በክልሉ በየደረጃው በሚገኙ መዋቅሮች የተጀመሩት ስራዎች ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል።

በክልሉ በህዝቡ የሚነሱ ችግሮችን ለመፍታት ከክልል ጀምሮ እስከ ቀበሌ በተካሄደው ጥልቅ የታድሶ ግምገማ የተለዩትን ጉድለቶች የመሙላት ሥራ በተፋጠነ መልኩ ወደ ተግባር ምዕራፍ መለወጥ እንዳለባቸውም ተናግረዋል።

ጥልቅ የተሃድሶ ግምገማ በክልሉ እየተካሄደ ያለውን የልማት፣ የመልካም አስተዳደርና የዴሞክራሲ ግንባታ ውጤታማ ለማደረግና የፀረ-ድህነት ትግሉን ለማፋጠን ጭምር ትልቅ ግብዓት እንደሆነም ገልጸዋል።

ምክር ቤቱ አዳዲስ ህጎችን በማወጣትና ከወቅቱ ጋር የማይጠጣሙትንም በማሻሻል የዜጎችን መብትና ነፃነት በዘላቂነት ለማረጋገጥ ተግባራዊነታቸውን በመከታተል ጉድለቶች እንዲታረሙ በትጋት እየሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።

ጉባኤው በሁለት ቀናት ቆይታው የክልሉን ማዕድንና ኤነርጂ ልማት ኤጀንሲ፣ የኮንስትራክሽን ቢሮ፣ የገቢ ግብር ፣የውሃና መስኖ ቢሮ ማቋቋሚያን ጨምሮ አስር ረቂቅ አዋጆችንና የተለያዩ ሹመቶችን መርምሮ እንደሚያጸድቅ ኢዜአ ዘግቧል። ( EBC)