አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 10 ፣ 2009 (GCDC) - በጋምቤላ ክልል ለሰፋፊ እርሻዎች ከተሰጠ 630 ሺህ ሄክታር መሬት ውስጥ ወደ ልማት መግባት ከነበረበት መሬት ወደ ስራ የገባው ከ15 በመቶ አይበልጥም ተባለ።
በሰፋፊ እርሻ ዘርፍ የሚታየውን ክፍተት ለመቅረፍ፥ ባለፈው አመት የካቲት ወር ጠቅላይ ሚኒስትር ሀይለማርያም ደሳለኝ በዘርፉ ላይ ያሉ ችግሮች ተለይተው እንዲጠኑ ትዕዛዝ አስተላልፈው የጋምቤላ ክልል ተመርጦ ጥናት ተደርጎበታል።
በጥናቱ 14 ባለሙያዎችን ጨምሮ የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር፣ የግብርና ኢንቨስትመንትና መሬት አስተዳደር ኤጀንሲ፣ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ እና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተሳትፈውበታል።
የጥናቱ ሪፖርት እንደሚያሳየውም በክልሉ በሰፋፊ እርሻዎች ላይ ያለው ችግር እጅግ ከፍ ያለ ሆኖ ተገኝቷል፤ ዘርፉም ውጤታማ አልሆነም ለማለት ያስደፍራል።
ከዚህ ቀደም ከ780 በላይ ባለሃብቶች በክልሉ እንደተሰማሩ ቢጠቀስም፥ በጥናቱ ግን በዘርፉ የተሰማሩ ባለሃብቶች ቁጥር 623 መሆኑ ተረጋግጧል፤ የቁጥሩ መዛነፍ ከመረጃ ልውውጥ ክፍተት የመጣ መሆኑም በጥናቱ ተጠቁሟል።
ከ630 ሺህ በላይ ሄክታር መሬት ውስጥ 15 ነጥብ 5 በመቶው ብቻ ወደ ልማት መግባቱ እንደተረጋገጠ፥ የግብርና ኢንቨስትመንትና መሬት አስተዳደር ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ አበራ ሙላት ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተናግረዋል።
ይህ ከዘርፉ ይጠበቅ ከነበረው አንጻር አነስተኛ ሲሆን፥ የባለሃብቶች አቅም በደንብ አለመታየቱ፣ በዘርፉ ላይ ያላቸው ልምድም ሆነ ብቃት ከግምት ውስጥ ከማስገባት አንጻር ከፍተት መኖሩም በጥናቱ ተረጋግጧል።
ከዚህ ባለፈም ባለሃብቶችን ከመደገፍ አንጻር ብዙ እየተሰራ አለመሆኑም ተጠቅሷል፤ በነጻ መሰጠት ያለባቸው መንግስታዊ አገልግሎቶችም እጅ መንሻ ስለሚጠየቅባቸው በሚፈለገው ፍጥነት መሄድ አለመቻሉም ነው የተነገረው።
ለባለሃብቶች የተሰጠ መሬት መደራረብም በጥናቱ በዋና ችግርነት ተነስቷል።
ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ከዚህ ቀደም በሰራው ዘገባ በክልሉ 43 ባለሃብቶች መሬት ተደራርቦ ተሰጥቷቸው በዚህ መሬት ላይም የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ብድር መስጠቱን መዘገቡ ይታወሳል።
በቅርቡ የተሰራው የጥናት ውጤት ደግሞ ከ623 ባለሃብቶች ውስጥ ለ381 ባለሃብቶች የተሰጠው ከ45 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ተደራርቦ እንደተሰጣቸው የሚያሳይ ሲሆን፥ በዚህ ሳቢያ በባለሃብቶች መካከል ግጭት እየፈጠረ ስራን በእጅጉ እንዳስተጓጎለ ተገልጿል።
በባንክ ለባለሃብቶች የተሰጠ ብድር ለታለመለት አላማ አለመዋሉም በዘርፉ ላይ ለታየው እጅግ አዝጋሚ አፈጻጸም ምክንያት መሆኑንም ነው አቶ አበራ የተናገሩት።
በክልሉ በግዙፍ እርሻ ኢንቨስትመንት ከተሰማሩ 623 ባለሃብቶች መካከል 200 ባለሃብቶች ከኢትዮጵያ ልማት ባንክና ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ብድር የተጠቀሙ ናቸው፤ በአጠቃላይም 4 ነጥብ 96 ቢሊየን ብር ተፈቅዶላቸዋል።
ብድሩ ለመሬት ልማት፣ ለማሽነሪ ግዥ፣ ለካምፕ ግንባታ እና ለስራ ማስኬጃ የተሰጠ ሲሆን፥ ከአጠቃላዩ ብድር ውስጥ 1 ነጥብ 99 ቢሊየን ብሩ ለመሬት ልማት ተብሎ ለ194 ባለሃብቶች ተሰጥቷል።
በዚህ ገንዘብ 314 ሺህ 645 ሄክታር መሬት እንዲያለሙ ቢጠበቅም ባለሃብቶቹ ያለሙት ግን 55 ሺህ ሄክታሩን ወይም ከሚጠበቀው 18 በመቶውን ነው፤ 47 ሺህ ሄክታሩ ደግሞ ገና በምንጣሮ ላይ ይገኛል ተብሏል።
በክልሉ ከሚገኙ 623 ሰፋፊ እርሻ አልሚዎች መካከል 242 ከቀረጥ ነጻ ተጠቃሚዎች ናቸው።
ባለሃብቶቹ 565 ትራክተር እንዳስገቡ ቢገልጹም 312 ትራክተር እንዲሁም አለ ከተባለው 731 ማረሻ 523 ብቻ መስክ ላይ መገኘቱ በሪፖርቱ ተመልክቷል።
እንዲሁም በክልሉ በኢንቨስትመንት ላይ አሉ የተባሉ 29 ባለሃብቶች በስፍራው አልተገኙም፤ ይህም ተጨማሪ ማጣራትን ይጠይቃል ተብሏል።
እነዚህ በዋነኝነት የተለዩ ችግሮች ናቸው፤ ለባለሃብቱ መሬት ከመተላለፉ በፊት ጥብቅ ማጣራት እንዲካሄድ ማድረግ ደግሞ በመፍትሄ አቅጣጫነት ተቀምጧል።
በዘርፉ ላይ ያልተገቡ አሰራሮች እንዲስተዋሉ አስተዋጽኦ የነበራቸው ሰዎችም እርምጃ እየተወሰደባቸው መሆኑ ተነግሯል።
ካለፈው አመት ጀምሮ በዘርፉ ላይ ጥናት እንዲደረግ በሚል የልማት ባንክ ብድር እንዲቆም ተደርጎ ነበር፤ አሁን ላይ ባንኮች አሰራራቸውን ፈትሸው ወደ ብድር እንዲመለሱ ተብሏል።
በተለይ ልማት ባንክ ሲሰጠው የነበረው ብድር በሁሉም ክልል ተቋርጦ ስለነበር ባለሃብቶች ላይ ጫና አሳርፎ ስለነበር አሰራሩ ተመርምሮ እንዲቀጥል ነው መንግስት የወሰነው። (ኤፍ ቢ ሲ)