ጋምቤላ፣ ሚያዚያ 08፣ 2009 (GCDC) - የጋምቤላ ህዝቦች አንድነት ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ጋህአዴን) ማዕከላዊ ኮሚቴ ጉባኤ የድርጅቱን ዋናና ምክትል ሊቀመንበር መረጠ።
የድርጅቱ ማዕከላዊ ኮሚቴ አመራሮቹን የመረጠው ትናንት ማምሻውን ባካሄደው አስቸኳይ ጉባኤ በጥልቅ ተሃድሶ ግምገማው የተሻለ አቅምና የጠራ አመለካከት ያላቸውን ነው፡፡
ኮሚቴው ቀደም ሲል የድርጅቱ ምክትል ሊቀመንበር የነበሩትን አቶ ጋትሉዋክ ቱትን ዋና ሊቀመንበር፥ አቶ ሰናይ አኮዎርን ደግሞ ምክትል አድርጎ በመመረጥ ሰይሟል።
የድርጅቱ አዲሱ አደረጃጀት የብሄረሰብ ስብጥርን ሳይሆን ብቃትን መሰረት ያደረገ እንደሆነም በመድረኩ ላይ ተገልጿል።
የድርጅቱ ሊቀመንባር ሆነው የተመረጡት አቶ ጋትሉዋክ ቱት፥ ድርጀቱ የጀመረውን ልማታዊና ዴሞክራሲዊ መስመሮች አጠናክሮ በማስቀጠል የህዝቡን የልማት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ይሰራል ብለዋል።
የህዝቦችን አንድነት ይበልጥ በማጠናከር በተለይም በወጣቱና በሴቶች ተጠቃሚነት ላይ በትኩረት እንደሚሰሩ ገልጸዋል።
እንዲሁም በመንደር የተሰባሰበውን ህዝብ ይበልጥ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት ተጠቃሚ ለማድረግ የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉም ነው ያሉት።
የድርጅቱ ምክትል ሊቀመንባር አቶ ሰናይ አኮዎር በበኩላቸው፥ የህዝቡን የልማት ተጠቃሚነት ለማጎልበት ድርጅቱ የጣለባቸውን ኃላፊነት በብቃት ለመወጣት እንደሚሰሩ ተናግረዋል።
የጋህአዴን ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኡኩን ኦቡያ ቀጣይነት ያለው የተሀድሶ ግምገማ በማካሄድ ድርጅቱን አቅም ባላቸውና የጠራ የአመለካከት መስመር በያዙ አመራሮች የመገንባቱ ሂደት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አንስተዋል።
እንደ ኢዜአ ዘገባ ማዕከላዊ ኮሚቴው በየሶስት የብሄረሰብ ዞኖች የተካሄደውን ጥልቅ የተሃድሶ ግምገማ ሪፖርት በመገምገም ጉባኤውን አጠናቋል። (ኤፍ.ቢ.ሲ)